Call: +25111249226 • +251118333094

E-mail: info@evasue.net

የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ተማሪዎችና ምሩቃን ማህበር (ኢቫሱ)
Evangelical Students’ and Graduates’ Union of Ethiopia

የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የቤተክርስቲያን አባላት

ካምፓስ ቆይታ በመንፈሳዊ ህይወት ለማደግ፣ ለአገልግሎት ዝግጅት ቁልፍ ስፍራ ነው። ምሩቃን በካምፓስ ቆይታቸው ይዘው የሚወጡት በሞያ ስልጠና ያገኙትን ድግሪ ብቻ ሣይሆን የከበረ መንፈሳዊ ዕውቀትና ልምድም እንደሆነ ይታመናል። ስለዚህ ምሩቃን  ለአጥቢያ ቤተክርስቲያን ትልቅ ሐብት ናቸው። በካምፓስ ቆይታቸው ያካበቱት መንፈሳዊ ዕውቀትና ልምምድ ለራሳቸው ብቻ ሣይሆን ለቤተክርስቲያንም ጠቀሜታው አያጠያይቅም። እንደ ተሰጣቸው የፀጋ ስጦታ በቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች በመሰማራት ራሳቸውን እና ሌሎችን ሊጠቅሙ ይችላሉ። በሰለጠኑበት ሞያም ቤተክርስቲያን እገዛቸውን በፈለገች ጊዜ በሙሉ የልብ ፈቃደኝነት ለማገልገል ዝግጁ እንደሚሆኑ ይታመናል። ምሩቃን እንደ አጥቢያ በቤተክርስቲያን አባል በመገልገልና በሚፈለጉበት የአገልግሎት ስፍራም የማገልገል የአባልነት ግዴታቸውን ይወጣሉ።

ይሁን እንጂ ምሩቃን የአጥቢያ ቤተክርስቲያን አባላት ከካምፓስ ቆይታ በኋላ ወደ ቤተክርስቲያን ሲመለሱ የሚገጥማቸው ተግዳሮት አይጠፋም። ለረጅም ጊዜ ከአጥቢያቸው በትምህርት ምክንያት ርቀው በመቆየታቸው እንግዳ የሚሆንባቸው ነገሮች ይኖራሉ፡-

  • የዕድሜ እኩዮቻቸው የሆኑትን የቀደሙ ጓደኞቻቸውን ወይም የአገልግሎት አጋሮቻቸውን የአለማግኘት ችግር።

ይህ ችግር ምሩቃን የሆኑ የአጥቢያ ቤ/ክ አባላት ፈጥነው ከሌሎች ቅዱሳን ጋር እንዳይቀላቀሉ ያደርጋቸዋል። ከዚህ የተነሣ የብቸኝነትና የባይተዋርነት ስሜት  ስለሚሰማቸው ከአጥቢያ ቤ/ክ የመራቅ አለዚያም መኖራቸው ሣይታወቅ በየፕሮግራሙ የሚገቡና የሚወጡ ብቻ ሆነው ይገኛሉ።

  • በካምፓስ ቆይታቸው ይዘውት የመጡት መንፈሳዊ ዕውቀት፣ልምምድና የአገልግሎት ከባቢን በቤ/ክ ያለማግኘት ችግር።

የቤተክርስቲያን የአገልግሎት አሰጣጥ ከካምፓስ የክርስቲያን ተማሪዎች ህብረት እንደሚለይ ባለመገንዘብ ምሩቃን ወደ አጥቢያ ቤ/ክ ሲመጡ አንዳንዱ ነገር እንግዳ ይሆንባቸዋል። የአሰራር ሰንሰለቱ ረጅም፣ የአመራር መዋቅሩ ውስብስብ፣የአገልግሎት ከባቢው (Atmosphere) ግራ የሚያጋባ፣ ወደ አገልግሎት ለመሰማራት የሚጠየቀው መስፈርትም የተንዛዛና አንዳንዴም አላስፈላጊ መስሎ ይታያቸዋል። አብዛኛው ነገር በስልጣን ተዋረድና በጥብቅ ኮሚቴ፣ የአገለግሎት በሮቹ ደግሞ በትላልቅ ቁልፍ እንደተቆለፈ ይሣልባቸዋል። ከዚህ የተነሣ ጥቂቶቹ በካምፓስ የለመዱትን ዓይነት መንፈሳዊ አደረጃጀትና የአሰራር ስልት የሚያገኙ እየመሰላቸው ምቹ የሚሉትን የአገልግሎት ዓውድ ፍለጋ  ከአጥቢያቸው ይሰደዳሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ማስተዋል በተሞላበት አካሄድ ነገሩን መዝነውና አስልተው የሚለወጠውን ለውጠው፣ ለችግሩ መፍትሄ የሚያመጣው የእነርሱ መለወጥ ከሆነ እነርሱ ተለውጠው፣ አንዳንዱን ጉዳይ ደግሞ አዛምደው በቤተክርስቲያናቸው እያገለገሉና እየተገለገሉ ይኖራሉ። ብዙ ጊዜ ሁለተኛውን ምርጫ የሚከተሉት ምሩቃን ግቢ ከመግባታቸውም በፊት ሆነ ከገቡ በኋላ ከአጥቢያቸው ጋር ያልተበጠሰ መንፈሣዊ ቁርኝት የነበራቸው ሆነው ይገኛሉ።

  • ምሩቃን የአጥቢያ ቤ/ክ አባላትን ተከታትሎ በአገልግሎት እንዲያዙ የሚያደርግ አገልጋይ ወይም ወጥ የሆነ አሰራር የአለመኖር ችግር።

ምሩቃን የአጥቢያ ቤ/ክ አባላት ከሶስት እስከ ስድስት ዓመት  በካምፓስ ቆይተው ሲመጡ የተረጋጋ የቤተክርስቲያን ህይወት እስኪጀምሩ ድረስ እገዛ ያስፈልጋቸዋል። ነገር ግን እንደ አሰራር አጥቢያ ቤ/ክ ይህን የሚያስፈጽም የአገልግሎት ዘርፍ ወይም የተመደበ አገልጋይ ላይኖራት ይችላል። ይህ ባልሆነበት ምሩቃኑ በካምፓስ ቆይታቸው የነበራቸውን የአገልግሎት ተሣትፎ ማወቅ አይቻልም። ከዚህ የተነሳ ምሩቃኑ በራስ ተነሳሽነት ወደ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች እስካልቀረቡ ድረስ አስተዋሽ ላይኖራቸው ይችላል።

  • ከምርቃት በኋላ ወደ ልዩ ልዩ ስራዎች ስለሚሰማሩ በአጥቢያ ቤ/ክ ህብረት ለማድረግ የጊዜ ማጣት ችግር።

ከካምፓስ ቆይታ በኋላ የምሩቃኑ ሌላው ችግር የሥራ ህይወትና የቤተክርስቲያን ህይወት ሚዛንን ጠብቆ ያለመሄድ ችግር ነው። ወደ ስራ ከተሰማሩ በኋላ ለመንፈሳዊ ህይወታቸው እንዲሁም በቤተክርስቲያን ለሚሆን የአገልግሎት ተሣትፎ የሚሰጡት ትኩረት አናሳ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ በቤ/ክ ለማገልገል ይቅርና ለመገልገልና ከቅዱሳን ጋር ህብረት ለማድረግ ተገቢውን ጊዜ መስጠት ይቸግራቸዋል። በሞያቸው ለሚሰሩት ስራ ከልክ በላይ የሆነ ትኩረት ይሰጡና ለመንፈሣዊ ህይወታቸው መታነጽና ለቤተክርስቲያን ተሣትፎ ያላቸው እይታ የተዛባ ይሆናል። የስራቸው ጉዳይ በአስፈላጊነት ቅደም ተከተል የመጀመሪያ ሲያደርጉት የመንፈሳዊ ህይወትና የቤተክርስቲያን ጉዳይ ሲመቻቸው የሚያደርጉት በአስፈላጊነቱም በሁለተኛ ደረጃ ያስቀምጡታል።

  • ከምርቃት በኋላ በስራ ምደባ ምክንያት ወደ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ከሄዱ በኋላ ከአጥቢያ ቤ/ክ ጋር ያላቸው ህብረት መቋረጥ።

ምሩቃን የሆኑ የአጥቢያ ቤ/ክ አባላት ከሚሰሩት ስራ ጋር በተያያዘ ወይም በሌላ ምክንያት ከአጥቢያ ቤተክርስቲያናቸው ሊርቁ ይችላሉ። ከሚሰሩት ስራ ጋር ተያይዞ ወደ ሌላ ሰፈር አልያም ወደ ሌላ የክልል ከተሞች ሊሄዱ ይችላሉ። እንዲህ አይነት ጉዳይ ሲገጥማቸው አባል ከሆኑባት አጥቢያ ቤ/ክ መልቀቂያ በመጠየቅ ወደ ሌላ አጥቢያ ቤ/ክ መሄድ ሲገባቸው ይሄንን ሣያደርጉ ይቀራሉ። በዚህ ጊዜ የሚሄዱበት አጥቢያ ቤ/ክ አባል አድርጋ ለመቀበል ከነበሩበት አጥቢያ ቤ/ክ መልቀቂያና የህይወት ምስክርነት ስላልያዙ ለመቀበል ትቸገራለች። ይህ ብቻ ሣይሆን አንዳንድ ጊዜ አባል ሊሆኑ ስለሄዱበት ቤ/ክ አስተምህሮና ልምምድ ሙሉ መረጃ ሣይኖራቸው ይቀርና ለስህተት ራሳቸውን አጋልጠው ይሰጣሉ።

ከነበሩበት አጥቢያ ቤ/ክ በተገቢው መንገድ በማሳወቅ ሣይለቁ ሲቀሩ ለአሣደገቻቸው ቤተክርስቲያን ተገቢውን አክብሮት ባለመስጠት ተወቃሽም ይሆናሉ። በቤተክርስቲያን መሪዎች ምርቃትና ፀሎት መሄድ ሲገባቸው ይህን ባለማድረግ የሚጎድሉበት በረከት ሊኖርም ይችላል።

 ከካምፓስ ቆይታ በኋላ ምሩቃን የአጥቢያ ቤተክርስቲያን አባላት ማድረግ የሚገባቸው ነገሮች በጥቂቱ፡-

  • ወደ ካምፓስ በሄዱ ጊዜ የነበሩ ጓደኞቻቸውን ተመርቀው በተመለሱ ጊዜ የማግኘት ዕድሉ ጠባብ ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ መረዳት።

ጓደኞቻቸው ወደ ዩንቨርሲቲ ባይገቡም በልዩ ልዩ የህይወት ጎዳናዎች ጉዞ እንደሚያደርጉ ማወቅ ይገባል። ስለዚህ ከአብሮ አደግነት፣ ከሰፈር ልጅነት፣ ከማህበራዊ ጓደኝነትና ከሌሎች ቅርርቦሽ የሚበልጠውን በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኙትን ወንድምና እህትነት አሻግረው ማየት ይጠበቅባቸዋል። የእግዚአብሔር ቤተሰብነት ጎልቶ ሲታየን ከሌሎች የቤ/ክ አባላት ጋር በመገልገልና በማገልገል ህብረት ለመፍጠር ነገሩ ቀላል ይሆንልናል።

  • የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ አደረጃጀትና የአሰራር ስልት ከካምፓስ የክርስቲያን ተማሪዎች ህብረት አሰራርና አወቃቀር እንደሚለይ ግንዛቤ መጨበጥ።

የአሰራር ልዩነት እንደሚኖር ከተረዳን በኋላ በአጥቢያ ቤ/ክ አሰራርና የአገልግሎት አደረጃጀት ውስጥ ገብቶ ለመስራት ራስን ማዘጋጀት ከምሩቃን ይጠበቃል። ምሩቃን በአጥቢያ ቤ/ክ ባለው ሁኔታ ለመገልገልም ሆነ ለማገልገል ዝግጁ ሲሆኑ እንደ ችግር የሚያዩአቸውን ነገሮች እንደ አገልግሎት ዕድል መቁጠር ይጀምራሉ። የማይመቹ ሁኔታዎችን ከሌሎች ወገኖች ጋር በመሆን የሚከፈለውን የጊዜ፣የቁስ፣የገንዘብና የዕውቀት ዋጋ ከፍለው ለማስተካከል ይጥራሉ። ምሩቃን ከልብ በሆነ መዘጋጀት በአጥቢያ ቤ/ክ ተሣትፎ ሲያደርጉ አንድ ሚስጥር ይገለጥላቸዋል። ይኸውም ምሩቃን ቤተክርስቲያን የምትፈልጋቸው ብቻ ሣይሆኑ ቤተክርስቲያን የምታስፈልጋቸው እንደሆነም ይረዳሉ።

  • በራስ ተነሳሽነት ወደ ልዩ ልዩ ህብረቶች መቀላቀልና ለአገልግሎትም ራስን ማዘጋጀት።

ምሩቃንን ከካምፓስ ቆይታ በኋላ ወደ አጥቢያቸው ሲመለሱ ተከታትሎ ወደ ተለያዩ ህብረቶች እንዲገቡ የሚረዳ ብሎም  እንደ የፀጋ ስጦታቸው ወደ አገልግሎት የሚያሰማራ አገልጋይ ወይም አሰራር በሌለበት የራስ የሆነ ተነሳሽነት ያስፈልጋል። ወደ ልዩ ልዩ ህብረቶች መግባት፣ እንደየፀጋ ስጦታዎች ወደ አገልግሎት ክፍሎች መቅረብና የሚጠየቀውን መስፈርት በማሟላት አገልግሎት መጀመር የምሩቃን ሃላፊነት ነው። ለምን ወደ ህብረት አልቀላቀሉኝም፣ ለምንስ የፀጋ ስጦታዬን አይተው ወደ አገልግሎት አላሳማሩኝም በሚል ራስን ከአጥቢያ ቤ/ክ ማግለል ወይም አጥቢያ ቤ/ክ መቀየር ፍጹም ስህተት ነው። ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካል ነች እኛ ደግሞ በአካሉ ውስጥ ብልቶች ነን። ሁላችንም እንደየፀጋ ስጦታችን በአካሉ ውስጥ የብልትነት ድርሻ አለን። ይሄንን ድርሻ ለመወጣት የሚያበረታታን ሰው ወይም አሰራር ቢኖር ጥሩ ነበር፣ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን ምሩቃን ራሳቸው ሃላፊነትን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

  • ምሩቃን የአጥቢያ ቤ/ክ አባላት ሚዛኑን የጠበቀ የስራና መንፈሳዊ ህይወት ሊመሩ ያጠበቅባቸዋል

መንፈሳዊ ህይወት በክርስቶስ ኢየሱስ አምኖ ለዳነ ሰው ቀዳሚ ጉዳዮ ነው። ከእግዚአብሔር የተሰጠውን የህይወት ዓላማ ለመፈፀም መንፈሳዊ ምግብ የሚመገብበት፣ ለአገልግሎት ትጥቅ የሚታጠቅበትና በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው ከዳኑ ቅዱሳን ጋር ህብረት የሚያደርግበት ስፍራ ደግሞ ቤተክርስቲያን ነው። የስራ ህይወትና መንፈሳዊ ህይወት አንዱ በሌላው አይተካካም። ሁለቱም ለምሩቃን ያስፈልጋሉ። ነገር ግን በአስፈላጊነት ቅደም ተከተል ስናስቀምጠው መንፈሳዊ ህይወት ከስራ ህይወት ይቀድማል። ስለዚህ ምሩቃን  ለመንፈሳዊ ህይወታቸውና በቤተክርስቲያን ለሚሆን ተሣትፎአቸው ተገቢውን ጊዜ መስጠት ይኖርባቸዋል። በሞያ የተሰማሩበት ስራ በመንፈሳዊ ህይወታቸው ለመድከም ብሎም በአጥቢያ ቤ/ክ ለሚኖራቸው ያለመሳተፍ ችግር እንደ ተጠቃሽ ምክንያት ሊቀርብ አይገባም። ከእግዚአብሔር ጋር ያለን የጠበቀ ህብረትና ጤናማ የሆነ የቤተክርስቲያን ህይወት ለሞያ ስራችንም እጅጉን አስፈላጊ እንደሆነ መረዳት አለብን።

  • ምሩቃን በልዩ ልዩ አሣማኝ በሆኑ ምክንያቶች አጥቢያ ቤተክርስቲያን ለመቀየር ሁኔታው ካስገደዳቸው ከቤ/ክ መልቀቂያ መውሰድ ይኖርባቸዋል።

ምሩቃን በሥራቸው ምክንያት ሰፈር ወይም ኣገር በሚቀይሩበት ወቅት ከቤ/ክ መልቀቂያ ይዘው መሄዳቸው ለራሳቸውም ሆነ ለአጥቢያ ቤ/ክ እጅጉን ይጠቅማል። የአሳደገቻቸው አጥቢያ ቤ/ክ አዲስ የሚገቡባት ቤተክርስቲያንን የአስተምህሮና የልምምድ ጤንነቷን በመፈተሽ ለስህተት እንዳይጋለጡ ታግዟቸዋለች። ከአሳደገቻቸው ቤ/ክ ጤናማ አስተምህሮና ልምምድ ወደ አላት ቤ/ክ መልቀቂያ ይዘው ሲሄዱ በቀላሉ ይቀበሏቸዋል። የህይወትና የአገልግሎት ምስክርነታቸው በመሸኛ ደብዳቤያቸው ላይ ስለሚገለጽ በሚቀላቀሉበት አጥቢያ ቤ/ክ ለመገልገልም ሆነ ለማገልገል  ዕድሉን ያገኛሉ። የአሳደገቻቸውን ቤ/ክ በተገቢው መልኩ ሲለቁ ለአጥቢያዋ ያላቸውን አክብሮት በማሳየታቸው ያለልብ ወቀሳ የማንም ልብ ሣያዝንባቸው ይሄዳሉ። ከዛም አልፎ በመሪዎች ፀሎት፣ ምርቃትና በረከት ስለሚሄዱ የእግዚአብሔር አብሮነት ከእነርሱ ጋር ይሆናል።

Latest Articles

Latest video